የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትና ተደራሽነትን የሚመጥን የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ሪፎርም መካሄዱ ተገለጸ - ብሔራዊ መረጃ ማዕከል

Nested Applications

የገቡ ህትመቶች

 

 

የገቡ ህትመቶች

ህትመቶች

Asset Publisher

null የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትና ተደራሽነትን የሚመጥን የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ሪፎርም መካሄዱ ተገለጸ

እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትና ተደራሽነት በሚመጥን ደረጃ የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፉን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

 

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘውና እንደ አዲስ የተደራጀው የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ የሪፎርም ሥራዎች በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ተጎብኝቷል።

 

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት፤ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከአቪዬሽን ደህንነት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ውስንነቶችን በተመለከተ ሰፊ ጥናት አድርጓል፡፡ በዚህ ጥናት መነሻነትም የአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት ሥራዎች ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ እንዲታጠቁ፤ ዘርፉን በሰው ኃይል ለማጠናከር እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ ቀልጣፋ የሴኪዩሪቲ አግልግሎት ለመስጠት እንዲቻል የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ በአዲስ መልክ ተደራጅቷል።

 

የሀገር መልካም ገጽታ ምልክት የሆነውንና እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትና ተደራሽነት በሚመጥን መልኩ የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ሥራን ለማዘመን በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ ተመስገን አብራርተዋል። የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ የአንድ የተወሰነ አካል ሥራ ብቻ ባለመሆኑ ቀደም ሲል በተደረገው ጥናት የተለዩ እጥረቶች ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያከናወኗቸው ማስተካከያዎችን በተመለከተ የደህንነት እና የሪፎርም ሥራ ኦዲት ማከናወን እንደሚገባም አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎ በኤርፖርቶች ያለው የደህንነት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻለ እና በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

 

አዲስ አበባ በጂኦ-ፖለቲካ አቀማመጧ የተነሳ ለደኅንነት ስጋት ተጋላጭ ብትሆንም በዘርፉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በኩል በመናበብ እና በቅንጅት የመሥራት ባህል በመዳበሩ እና በተሰጠው ልዩ ትኩረት እስካሁን አደጋ እንዳላጋጠመ አብራርተዋል። በጉብኝቱም የአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ በአደረጃጀት፣ በአሰራር ስርዓት፣ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ጥሩ አቋም ላይ እንደደረሰ መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አየር መንገዱ የበኩሉን አስተዋፅዖ እና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

 

የአቪዬሽን ደህንነት ቁልፍ ከሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ያመለከቱት ደግሞ በጉብኝት መርሐግብሩ የታደሙት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር / አብርሃም በላይ ናቸው፡፡ ዘርፉ ከደኅንነት አንፃር ብቻ ሳይሆን በሀገር ኢኮኖሚ፣ ገጽታ እና ሌሎች መስኮች የሚያመጣውን ሁለንተናዊ ተጽዕኖ ታሳቢ ያደረገና ወደፊት አንድ እርምጃ የተራመደ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

 

የአቪዬሽን ደህንነት በተሟላ መንገድ እየተረጋገጠ ደንበኞችን በሚያስደስት መልኩ መሰራት እንዳለበት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ የአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ራስን የማዘመን እንዲሁም የቅንጅት ሥራዎች የማያቋርጡና ወደፊትም የሚቀጥሉ ተግባር መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዳመለከተው፤ የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ ያለፉት 14 ወራት የሪፎርም ሥራዎች በተጎበኘበት መርሐግብር በዘርፉ በቅንጅት የሚሠሩ የተለያዩ አካላት የጀመሯቸው ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ በጋራ ተናቦ እና ተቀናጅቶ የመሥራት ባህል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡