70 የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

70 የተለያዩ የውጭ ሃገራት ዜጎች ኑራቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ አድርገው በህገወጥ የዶላር ዝውውር ሲሳተፉ በተደረገ ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል እንደተደረሰባቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ።

 

ተጠርጣሪዎቹ ከውጭ ወደ ሃገር ቤት የሚላክ ዶላር፣ ዩሮ እና የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦችንም በየሀገራቱ ለዚሁ ዓላማ ባስቀመጧቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ወደ ግል አካውንታቸው እንዲገባ በማድረግና የኢትዮጵያ የብር ኖቶችን በመስጠት በህገወጥ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ተግባርም ጭምር በመሳተፋቸው ተጠርጥረው ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ገልጿል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት የሠጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እና ከህገወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ህገወጥ የመኖሪያ ፈቃድን እና ፓስፖርትም ጭምር አጭበርብረው ሲሰጡ የነበሩ 36 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።

 

በአዲስ አበባና ሃዋሳ ከተሞች በኢሚግሬሽንና ኤርፖርት አካባቢዎች ላይ ተመድበው ሲሰሩ ከህገወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር የግል ጥቅማቸውን ሲያግበሰብሱ የነበሩ ሰራተኞችና ሃላፊዎች እንዲሁም ህገወጥ ደላሎች በተደረገ ጥብቅ ክትትልና የህዝብ ጥቆማ ከሲዳማ ክልላዊ መንግስት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላካው መግለጫ ጠቁሟል።

 

መግልጫው አክሎም፣ ተቋሙ በምስራቅ ኢትዮጵያ በድሬዳዋ አካባቢ በህገወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎች ላይ ያደረገውን ጥልቅ ጥናት መሰረት በማድረግ፤ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የተቀናጀ ኦፕሬሽን በማካሄድ ግምታቸው 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚሆኑ የማዕድን ምርቶችን 11 ህገወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን አመልክቷል።

 

በተያያዘ በህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ በመሰማራት ግምታቸው 70 ሚሊዮን ብር የሆኑ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን፣ ልባሽ ጨርቆችን፣ የሲጋራ ምርቶችና መሰል ቁሳቁስንም 11 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉ በመግለጫው ተጠቅሷል።

 

በተጨማሪም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት አስፈላጊውን መረጃ በመሰብሰብ ከፌደራልና ከክልል ፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግም በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 582 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ 58ሺህ ዩሮ፣ 10ሺህ ፓውንድ፣ 5 ሺህ 530 የካናዳ ዶላር፣ 67 ሺህ 145 የሳውዲ ሪያል እንዲሁም 2 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ እና 10 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ወርቅ ከበርካታ ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን ገልጿል።

 

አገልግሎቱ መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ባለፉት ወራት ከፌደራልና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በተካሄዱ ተከታታይ ኦፕሬሽኖች በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከልም ከህወሃት የሽብር ቡድን ተልዕኮ በመውሰድ ለቡድኑ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ 33 ተጠርጣሪዎች፤ እንዲሁም እየተወሰዱ ባሉ የህግ ማስከበር እርምጃዎች 200 በላይ የሸኔ የከተማ ህዋስ አባላት ወይንም ተላላኪዎች ሲያዙ፤ ለቡድኑ የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ 20 ግለሰቦች የባንክ የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውቋል።

 

የጽንፈኝነት አስተሳሰብን በማራመድ የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ የሃሰትና የውሸት ወሬዎችን በመዝናት ሁከትና ግርግር ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩ 42 ተጠርጣሪ ግለሰቦችም መያዛቸውን አመልክቷል።

 

መግለጫው አክሎም፤ ሃገሪቱ ህገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ዝውውር ለመቆጣጠርና ለመከላከል ያወጣችውን አዋጅ መሠረት በማድረግ በተከናወኑ የተቀናጁ የኦፕሬሽንና የፍተሻ ሥራዎችም 11 ብሬን የቡድን የጦር መሣሪያዎች 524 የተለያዩ የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች፣ 31 ሽጉጦችና 25 ሺህ 656 የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶች ከበርካታ ተጠርጣሪዎች ጋር በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል።

 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሃገርን ሉዓላዊነትና አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ፣ ከፌደራልና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሽብርተኞቹ፣ በታጣቂዎች እንዲሁም በተለያዩ ህገወጥ ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጾ፤ ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት የአገልግሎት መስሪያ ቤቱን ነፃ የስልክ ጥሪ 910 በመጠቀም እንደተለመደው ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች