ወደ መቀሌ እና ሽሬ በሚደረጉት በረራዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ወደ መቀሌ እና ሽሬ በሚደረጉት በረራዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ እና ሽሬ በሚያደርጋቸው በረራዎች በአዲስ አበባ እና በመቀሌ ተመድበው የሚሠሩ አንዳንድ ባለሙያዎችና ከአየር መንገዱ ጋር የሚሠሩ ኤጀንቶች ጉዳይ እናስፈጽማለን ከሚሉ ግለሰቦች ጋር ተመሳጥረው ከተቀመጠው የክፍያ ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ስለተደረሰባቸው ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢፕድ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉና ኅብረተሰቡን ለእንግልት ሲዳርጉ የተደረሰባቸው በሙሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ በጋራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በቀን ወደ መቀሌ የሚደረገው የበረራ ቁጥር ወደ አምስት ማደጉን እንዲሁም ወደ ሽሬ የሚደረገው በረራም በሳምንት ወደ ዘጠኝ ከፍ ማለቱን የጠቆመው መግለጫው፤ አስፈላጊው የሰው ኃይል በየበረራ መዳረሻው ተመድቦም ደኅንነቱ በተረጋገጠ ሁኔታ ተጓዦች በቂ አገልግሎት እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

ሆኖም በርካታ ሰዎች የአየር ትራንስፖርት የመጠቀም ፍላጎታቸው መጨመሩን እንደመልካም አጋጣሚ የወሰዱት በአዲስ አበባ እና በመቀሌ የተመደቡ ሙያዊ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዳንድ ሠራተኞችና ከአየር መንገዱ ጋር የሚሠሩ ኤጀንቶች ከጥቅም ተጋሪ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ከተቀመጠው የክፍያ ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ እንደነበር ተደርሶበታል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮያ አየር መንገድ በጉዳዩ ዙሪያ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው በድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩ አራት ግለሰቦች በመለየታቸው እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጉዳያቸው መቀሌ ፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኝ መግለጫው አስታውቋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሢሠሩ የነበሩ አምስት ኤጀንቶች ከሥራ ታግደው ጉዳያቸው እየተጣራ ሲሆን፤ ሌሎች በጉዳዩ የተሳተፉ አካላትን በመለየት እርምጃዎች ለመውሰድ መረጃዎችን የማጠናቀር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡

ኅብረተሰቡ በሕጋዊ አሠራር እና ይህንኑ ለማከናወን ከተደራጀ ቢሮ ብቻ ቀርቦ ትኬቱን በመቁረጥ በተቀመጠው የተቋሙ ታሪፍ ብቻ አገልግሎት ማግኘት የሚችል መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ባልተገባ መንገድ በሕገ-ወጦች ተታሎ እላፊ ገንዘብ እንዳይከፍልና እንዳይጭበረበር መጠንቀቅ እንዳለበት አስገንዝቧል።

ከዚህ ውጭ ኅብረተሰቡ በማንኛውም ሁኔታ ለማጭበርበር የሚሞክሩ ግለሰቦች ሲያጋጥሙት በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ እና የደኅንነት አካላት መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረበው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ በተቋሙ ነፃ የስልክ መስመር 910 ጥቆማ መስጠት እንደሚቻልም ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል።

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች