የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አጭር የኋላ ታሪክ

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አጭር የኋላ ታሪክ

በአፄ ሀይለሥላሴ  ዘመን

የመረጃና ደህንነት ስራ በኢትዮጲያ የተጀመረው በአፄ ሐይለስላሴ ዘመን ከ1937-1955ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን በወቅቱ በነበረው የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር “የፀጥታ ጠቅላይ መምሪያ” በሚል ተቋቁሞ የአገርና የሕዝብን ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮ ተሰቶት ይሰራ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ የአርበኞችን ተቃውሞ መከላከል፣ጣልያኖች በዘረጉት የክልሎች የከፋፍለህ ግዛ በተፈጠሩ የክልላዊ አስተዳደሮች ሊነሱ የሚችሉ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠርና ከጣልያን ወረራ በኋላ የነበረውን አለመረጋጋት መቆጣጠር ዋነኛው ተግባሩ ነበር፡፡

በተጨማሪም የፀጥታው ጠቅላይ መምርያ በወቅቱ በነበሩ የስጋት ትኩረቶችን መሰረት አድርጎ በመዋቅሩ የእስልምና ክፍል፣  የኮሚኒስት ክፍል፣ የአየር መቆጣጠር ክፍል ፣የአረብ ክፍል  እና  የምስራቃውያን ክፍል  የሚባሉ አካሎች ነበሩት፡፡

በ1953 ዓ. ም. በነበረው የመፈንቀ ለመንግስት ሙከራ በኋላ ግን ተቋሙ አወቃቀሩን  በሁለት  በመክፈል በአገር ግዛት ሚኒስቴር ስር የህዝብ ፀጥታ ጥበቃ ድርጅት ፤ እና በንጉሱ ፅ/ቤት ስር የግርማዊ ንጉሰ ነገስት ልዩ ካቢኔ  በሚል እንደገና ተዋቅሯል፡፡ የህዝብ ፀጥታ ጥበቃ ድርጅት ተልዕኮ የስለላና ፀረ-ስለላ ስራ  ሲሆን የንጉሰነገስቱ  ልዩ ካቢኔ ተልዕኮዎች ደግሞ የካቢኔ አባላቱን ፤ የሰራዊት ሀላፊዎችን  መከታተል፣በህዝቡና በሰራዊቱ የሚነሱ ተቃውሞዎችን መሰለልና መከታተል እና የውጪ  ስለላ መስራት ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በንጉሱ ዘመን የተጀመረው የደህንነት ሥራ የአገርንና የሕዝብን ፍላጎት ያማከለ ሳይሆን በይበልጥ ለንጉሱ ዘብ በመቆም ስልጣናቸውን ለማራዘም  ያለመ ነበርነበሩት(NISS ,2011) በንጉሱ ስርአት ግዜ የሕዝብ ግንኙነት ስራ በደህንነት ተቋሙ ውስጥ በመዋቅር ተካቶ ለመተግበሩ ምንም መረጃ አያሳይም፡፡

በደርግ መንግስት ዘመን    

ደርግ በ1966 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም የነበረውን የንጉሱን ዘመን የመረጃና የደህንነት ተቋም በማፍረስ የራሱን በደርግ ፅ/ቤት የመረጃ ማመዛዘኛና ማከፋፈያ ኮሚቴ በሚል አቋቋመ፡፡ የዚህ ተቋም  ተልእኮ በወቅቱ የነበረውን የሶማሊያ ሁኔታ መከታተልና ፀረ-አብዮተኞችና  የኢምፔርያሊስቶች ቅጥረኛ የሚባሉ ሀይሎችን መከታተል ነበርነበሩት(NISS ,2011)፡፡

ከ1972 ዓ.ም. በኋላ የደህንነት ተቋሙ ለመጀመርያ ግዜ የአገርና የህዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስቴር በሚል በአዋጅ እንደገና  ተቋቋመ፡፡ መስሪያቤቱ የደህንነትና የመረጃ ስራዎችን አጣምሮ በመስራት ተቋማዊ መልክ መያዝ የጀመረበት ግዜ ሲሆን ተቋሙ በወቅቱ የነበረው አደረጃጀት፡-የውስጥ ደህንነት ድርጅት፤የውጪ አገሮች ጥናትና ምርምር ድርጅት፤የኢኮኖሚ ደህንነት ድርጅት፤የኢምግሬሽንና የይለፍ ጉዳይ ድርጅት፤የስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር፤የወታደራዊ ደህንነት (በሰራዊቱ አመፅ እንዳይነሳ የሚከታተል)፤ልዩ ጥበቃና እስትራተጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት (ማሰልጠኛ) የሚባሉ ነበሩ ሲሆን የተቋሙ ተልዕኮም በወቅቱ የነበረውን የፀረ-ደርግ ተቃውሞ ትግል መከታተል ነበር፡፡

ከ1980-1983ዓ.ም የኢህዴሪ መመስረትን ተከትሎ ተቋሙ ሰፊ ስልጣን ተሰጥቶት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚል በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተደረጎ፤ ቀድሞ ከነበሩት ክፍሎች በተጨማሪ የፖሊስ ሰራዊት፤ወታደራዊ ኮሚሳርያት፤ወህኒቤቶች አስተዳደር እንዲካተቱ ተደርጎ እስከ 1983ዓ.ም መጨረሻ ዘለቀ፡፡ በዚህ በአዲሱ መዋቅር የነበረው ተልዕኮም በጎረቤት ሃገራትን ጨምሮ በውጪ ሃገራት የስለላ ስራ መስራትና፤ በውስጥ ከህዝቡም ሆነ ከሰራዊቱ ሊነሳ የሚችል ተቃውሞና አመፅ በማፈን   የስርዓቱን ህልውና መጠበቅ ነበር፡፡  ከዚህ መረዳት እነደሚቻለው በደርግ ዘመን የነበረው የደህንነትና የመረጃ ስራ የፖለቲካ አቋም ይዞ ደርግን በስልጣን ላይ ለማቆየት ብቻ ሲሰራ እነደ ነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በኢፌዴሪ መንግስት ጊዜ

የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ የሽግግሩ መንግስት የነበረውን የደርግ የመረጃ ተቋም አደረጃጀት በአዋጅ እንዲፈርስ ካደረገ በኋላ ከአደረጃጀቱ የፖሊስ ሰራዊት፣ ማእከላዊ ምርመራና ወህኒቤት ከተቋሙ እንዲወጣና ወታደራዊ ኮሚሳርያትና ወታደራዊ ደህንነት ክፍሉ እንዲፈርስ ተደርጎ በነበረው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚል ስያሜ ቀጥሏል፡፡ ተቋሙ በሽግግሩ አመታት (ከ1983-1987ዓ.ም) የስርዓት ለውጡን ተከትለው የመጡ የፀጥታ ችግሮችን ለማስወገድና በሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ተልዕኮው ነበር ፡፡

በመቀጠልም  በ1987 ዓ.ም. ተቋሙ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ ስያሜውም የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን በሚል በአዋጅ ቁ6/1987 እንደገና የተቋቋመ ሲሆን ተልዕኮም፡-

  • በአገር ውስጥና በውጪ የአገርና የህዝብ ደህንነት ጥበቃ  ስራ መስራት፤
  • የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ፖሊሲ ማዘጋጀትና ሲፈቀድ ተግባራዊ ማድረግ፤በአገር ነፃነትና ኢኮኖሚ የሚጠነሰሱ ሴራዎችን መከታተል፤ማጣራትና ለሚመለከተው ማሳወቅ፤እና
  • ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበር የኢሚግሬሽንና የስደተኞች አገልግሎቶችን መስጠት  የሚሉ ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡

የዓለምን የማያቋርጥና ፈጣን የኢኮኖሚ፣የፖለቲካና ማህበራዊ ለውጥ  ከግምተ በማስገባት አገራችን  ከለውጡ ጋር  ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና ስጋቶችን ለመቋቋም እነዲሁም ለመከላከል ጠንካራ የደህንነትና የመረጃ ተቋም ለመፍጠር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አግልግሎት በ2005 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 804/2005 እንደገና ተቋቁሟል፡፡ ይህም  የሀገሪቱን የሰላም፡ የልማት፡ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስርአት ግንባታ ይደግፋል ተብሎ ታምኖበት ነበር፡፡

ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠዉን ስልጣንና ተግባር የመረጃና ደህንነት ተልዕኮዎችን መፈፀም ሲሆን በመረጃ ረገድ ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በህገወጥ መንገድ ለማፍረስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የመከታታል እንዲሁም በየአካባቢዉ የሚነሱ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ መረጃ በማሰባሰብና ጥልቅ ትንታኔ በማድረግ ለመንግስት የስራ ሀላፊዎች  የውሳኔ ሓሳብ ማቅረብ ነው፡፡

በሌላ በኩል በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም አይነት ሴራዎችና ስጋቶችን በተለይም ደግሞ ከሽብርተኘነት፣ ከአክራሪነትና፣ ፅንፈኝነትጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ የስጋት አዝማሚያዎችን አስቀድሞ በመገመት የመከላከል ስራዎችንም ይሰራል፡፡

በአጠቃላይ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በሀገሪቱና በዜጎቿ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም  ስጋቶች የማጥናት፤ጉዳት ሳያደርሱ ቀድሞ የመከላከል ስራዎችን ያከናዉናል፡፡ በደህንነት መስክም ለቁልፍ ተቋማትና ባለስልጣናት ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ከአቬሽን ደህንነት ባለፈም ለግዙፍ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችም ተገቢዉን ፍተሻና ጥበቃ ማድረግ የተቋሙ የደህንነት ስራዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ለመረጃና ደህንነት የሚያገለግሉ ማንኛቸውም አይነት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ላይም ደረጃ የማውጣትና የጥራት ስራዎችን ከመስራት ባሻገር ፍቃድ የመስጠት ስራዎችንም ያከናዉናል፡፡

ተቋሙ በዋነኝነት የህዝቦችንና የሀገሪቱን የደህንነትና የፀጥታ አደጋዎች አስቀድሞ የማየትና የመተንተን መንግስት አደጋዎችን አስቀድሞ እንዲከላካልና መልካም አጋጣሚዎች ካሉ በአግባቡ ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ሊዉሉ የሚችሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራዎችን እንዲሰራ ያደርጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአዋጅ በተሰጠዉ ስልጣንና ተግባር በሀገሪቱ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የዉጭ ወረራዎች እንዲቀለበሱ ከማድረግ ባለፈ በተለይም ደግሞ ከሽብርተኝነትና ፅንፈኝነት ጋር በተያያዘ የሽብር ቡድኖች በህዝብና በሀገር ላይ ሊፈፅሙ የሚችሉትን ጥቃትና አደጋ አስቀድሞ ከመከላከል ረገድ ዉጤታማ ተግባራትን አከናውኗል፡፡

የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሊጎዱ የሚችሉ አደጋዎችንም ከመከላከል አንፃርም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ቁልፍ የመንግስት ተቋማትና ባለስልጣናትን የደህንነት አደጋ እንዳያጋጥማቸዉ በማድረግ በኩልም ተቋሙ ተልኮዉን በብቃት ፈፅሟል፡፡ ሀገሪቱ የአፍሪካ መዲና አንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችና ጉባኤዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ የደህንነት ስራዎች በተቋሙ ተከናውነዋል፡፡

ከመጋቢት 2010 ዓም በኋላ

ተቋሙ ያሉበትን ድክመቶች አስቀርቶ ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ሥርአቱን በተከተለ መልኩ የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሳይጋፋ ከላይ የተጠቀሱትን አላማዎች በብቃት እንዲያሳካና ተቋሙ በየትኛውም ደረጃ መደበኛና ልዩ ተልዕኮውን በተጠያቂነት እንደሚሰራ በ2011 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ተረጋግጧል፡፡

ከየካቲት 2010 ዓ.ም. በፊት አንድ አንድ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት ማስፈጸም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ሲገባቸዉ ዜጎች  በፖለቲካ አመለካከታቸዉ በአስተሳሰብና በአመለካከት ልዩነታቸዉ ኢ߻ሰብአዊ ድርጊቶች ደርሶባቸዋል በሚል በህብረተሰቡ ለተቋሙ መልካም አመለካከት አልነበረውም፡፡ በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነትም በአገልጋይና ተገልጋይ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ከመሆን ይልቅ በጥርጣሬና በስጋት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡

ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ባለመሆኑ ምክንያት በሽብርተኝነትና ፅነፈኝነት ሽፋን ዜጎችን ሲያስር፡ ሲያንገላታና ሲመረምር ነበር በሚል በህብረተሰቡ ዘንድ የሚወደድ፡ የሚከበርና የሚታመን ተቋም መሆን ሲገባዉ የሚፈራ ሆኗል፡፡ ከዚሁ በመነሳት ተቋሙ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ ሆኗል የሚሉ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡ ሚስጢራዊነትን ተገን በማድረግ በመገናኛ ብዙሃን በኩል ይፋ ሊሆኑ የሚገባቸዉ መረጃዎች አለመገለፃቸዉ የተቋሙን የግልፀኝነት ጉዳይ ጥያቄ ዉስጥ አስገብቶት ቆይቷል፡፡

ተቋሙ ከላይ ከተጠቀሱትን ችግሮች ተላቆ ሕገ መንግስታዊ ወደ ሆነው አሰራር ለመግባት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በሚከተለው ሪፎርም የማንም የፖለቲካ ወገን ደጋፊ ሳይሆን ተጠያቂነትን ባማከለ መልኩ የህዝቡን፣የመንግስትን፣ የሁሉንም ፖለቲካ ፓርቲዎችና ፣ የዲፕሎማሲ መህበረሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ የሃገር ኩራት ለመሆን እየሰራ ነው፡፡