በአዲስ አበባ የሽብርና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመፈጸም ሙከራ በሚያደርጉ ኃይሎች ላይ እተወሰደ ያለው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት፣ በአዲስ አበባ እና አዋሳኝ አካባቢዎች የተከናወኑ የመረጃ ሥምሪቶች ሪፖርት በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ቀርቦ ምክክር ተካሂዶበታል።

 

በመድረኩ ላይ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሑሴንን ጨምሮ የፌዴራል የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት፣ የፍትሕ ተቋማት እንዲሁም የክልል የጸጥታ ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

በዚህ መድረክ፣ የፀረ ሰላም ኃይሎችን የተደራጀ ሤራና ሌሎችንም ሕገ ወጥ ተግባራትን በመከላከልና በማክሸፍ ረገድ ስኬት መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡ ይህም የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በመናበብና በተቀናጀ መንገድ ሥምሪት በማከናወናቸው የመጣ መሆኑ ተገልጧል።

 

በተለይ በአማራ ክልል በፋኖ ስም ሲንቀሳቀስ የነበረው ጽንፈኛ ኃይል በሀገር መከላከያ ሠራዊት እየደረሰበት ያለውን ጠንከር ያለ ምት መቋቋም አቅቶት ሲበታተን የሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የስበት ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ የጥፋት ተልዕኮው ማስፈጸሚያው ለማድረግ በኅቡዕ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፣ የቡድኑን ሰንሰለት ለመበጣጠስ መቻሉን መረጃው ጠቁሟል፡፡

 

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል እየሞከረ ባለዉ የሸኔ የሽብር ቡድን ላይ የተወሰደዉ ርምጃ የቡድኑን አከርካሬ በመስበር ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራዎች እንዳደረሰበት ተነግሯል። 

 

ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ትሥሥር ያላቸዉ ቡድኖች በአዲስ አበባና አካባቢዋ ላይ ዝርፊያ፣ እገታና ሌሎች የተደራጁ ወንጀሎችን ለመፈጸም በኅቡዕ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም፣ በጸጥታና ደኅንነት አካላት በተሠራ የተቀናጀ ክትትልና ኦፕሬሽን መክሸፉን የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ አመልክቷል። 

 

በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 174 በላይ ግለሰቦች ከተቀጣጣይ ፈንጂዎችና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን አመልክቷል።

 

በተጨማሪም ሕዝብን በማማረር፣ በመመዝበርና ከጥፋት ኃይሎች ጋር በመተባበር ተግባር የተሠማሩ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በባንኮች፣ በፍትሕ አካላት እና በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ ግለሰቦችን በመረጃ ሥምሪትና ክትትል በመለየት በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑም ተገልጧል፡፡ 

 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ የጋራ ኦፕሬሽኖች በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ በሽብር፣ በተደራጀ ስርቆት፣ በዝርፊያ እና በእገታ የወንጀል ተግባራት ላይ የተሠማሩ የጥፋት ኃይሎችን አከርካሪ ለመስበር እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህም አንጻራዊ ሰላም እንዲፈጠርና ኅብረተሰቡ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲገባ ማገዙን ጠቁመዋል፡፡ 

 

የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በውስጣቸው ያሉትን ክፍተቶችና ውሱንነቶች እያረሙ የላቀ የመፈጸም ዐቅም እንዲላበሱ የሚያስችሉ ሥራዎችን አጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ተመሳሳይ መድረኮችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡ 

 

የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በቀጣይም የተደራጁ ወንጀሎችን፣ ሽብርተኞችንና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በጥናት ላይ በመመሥረት ለመከላከል የሚያግዙ ሥምሪቶች እንደሚያከናውኑ በመድረኩ የገለጹት ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው። 

 

አምባሳደር ሬድዋን እንዳሉት፦ ተልዕኮን በብቃት ለመወጣትና በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ የሚፈጥሩ ሥጋቶችን ለማስወገድ በቅድሚያ ሁሉም ተቋም ራሱን እያበቃ፣ እየፈተሸ፣ እያጠራ የመሄድ አስፈላጊነት ላይ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡

 

መድረኩ በርካታ መልካም ተሞክሮዎች የተገኙበት መሆኑን የገለጹት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን፤ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ ራሳቸውን ከብልሹ አሠራር ለማጽዳት፤ የአባላቱን ሥነ ምግባር በቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም የሕዝብ አለኝታነታቸውን ለማስቀጠል የጀመሩትን ሪፎርም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተባበረና በተናበበ አኳኋን ተመሳሳይ መድረኮችን ማካሄዳቸውን እንደሚቀጥሉ መጠቆማቸውን መረጃው አስታውቋል፡፡

 

በመረጃና በደኅንነት ተቋማት መካከል የሚደረገው የመረጃ ልውውጥና ሁለንተናዊ መደጋገፍ ሀገራዊ ሰላምንና ደኅንነትን በሚያረጋግጥ አግባብ እንዲመራ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንና ተመሳሳይ መድረኮችም እየተዘጋጁ አፈጻጸሞች እንደሚገመገሙ አምባሳደር ሬድዋን መናገራቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች