የኢትዮጵያ እና የኬኒያ የመረጃ ተቋማት የሽብር ቡድን አመራሮች እና ታጣቂዎች ላይ የጀመሩትን ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የኢትዮጵያ እና የኬኒያ የመረጃ ተቋማት በድንበር አካባቢ እና በኬኒያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድን አመራሮች እና ታጣቂዎች ላይ የጀመሩትን ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡  

 

በኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ የተመራ የልዑካን ቡድን ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡       

 

ዳይሬክተር ጄነራሉ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደረሱ የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።   

 

የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዳመለከተው፤ የሁለቱ ሀገራት አቻ የመረጃ ተቋማት ከዚህ በፊት በመረጃ ልውውጥ እና በሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ወደ ሥራ መግባታቸውን እና በትብብራቸው መሰረትም የተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎቸና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እየተገናኙ ሲገመግሙ ቆይተዋል፡፡    

 

በዚሁ መሰረትም የኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ ከተቋማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በበርካታ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት እና ግምገማ በማድረግ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማስቀመጣቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላከልን መረጃ ጠቁሟል፡፡     

 

ሁለቱ ሀገራት ድንበር እንደሚጋሩት ሁሉ የሚጋሯቸው የደኅንነት ስጋቶች እና አብሮ የመልማት አጀንዳዎች እንዳሏቸው በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል። በአሁኑ ወቅትም በሁለቱ ሀገራት ድንበርና በኬኒያ ውስጥ ገባ ወጣ እያለ የተለያዩ እኩይ ተግባራትን የሚፈጽመውን የሸኔ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴን ለመግታት በሚቻልበት መንገድ ላይ መክረዋል። 

 

ቡድኑ በተለይም ሲፈጽማቸው የነበሩ ዜጎችን የማገት፤ ንብረት የመዝረፍ፣ የማውደም እንዲሁም የሰዎችን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ሥራዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኬኒያ ዜጎችንም ጭምር ችግር ላይ የጣለ መሆኑ እና ይህን እኩይ ዓላማውን ለማክሽፍ እና ለመግታት የጀመሩትን የመረጃ ልውውጥ እና የተቀናጀ ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመልክቷል፡፡

 

በተጨማሪም ቡድኑ የተሰማራበቸውን የኮንትሮባንድ ንግድ፤ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፤ ህገወጥ የማዕድን ማውጣትና ማዘዋወር ሥራዎችን ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው በውይይት ወቅት መገለፁን ጠቁሟል፡፡   

 

በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች እና በኬኒያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ የሽብር ቡድን በቅርቡ ሁለት የኮሪያ ዜጎችን በማገት ለአልሸባብ አሳልፎ መስጠቱ፤ ቡድኑ በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው መሆኑን ያመለከተው መረጃው፤ ሁለቱ የሽብር ቡድኖች በአካባቢው እና በቀጠናው የደቀኑትን የሽብር ስጋት በጋራ ለመከላከልና ለመቀልበስ መወሰናቸውን የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ አመልክቷል፡፡ በአካባቢው እና በቀጠናውም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እያካሄዱ ያሉትን የመረጃ ልውውጥና የተቀናጀ ኦፕሬሽን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።  

 

በተያያዘ ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት በሱዳን ያለው ጦርነት እና አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታና ሱዳን ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ እንድትመለስ በጋራ እንደሚሰሩም መግለፃቸውን የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ ያስረዳል፡፡ የሁለቱም ሀገራት ድንበር ተጋሪ በሆነችው ደቡብ ሱዳንም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና የተረጋጋች እንድትሆን በጋራ የማገዝ ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። 

 

የወቅቱ ስጋት በሆነው የሳይበር ደኅንነት ላይም በጋራ የጀምሩትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጋራ ግንዛቤ ይዘዋል። በቀጣይም ሊደርስ የሚችል የሳይበር ጥቃትን በጋራ የመከላከልና የማስቆም የተቀናጀ ሥራም ለመስራት ተስማምተዋል። የሀገራት አሁናዊ ስጋት እየሆነ ያለውን የስነ-ልቦና ጦርነትንም ለመከላከል እና መልሶ ለማጥቃት በሚደረግ ጥረት ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተመልክቷል።    

 

በመጨረሻም በኬኒያ የመረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ኑረዲን መሐመድ ሀጂ የተመራው ልዑክ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን እና የዓድዋ መታሰቢያን የጎበኙ ሲሆን ፤ከጉብኝቱ በኃላም ዳይሬክተር ጄነራሉ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአፍሪካ ህብረት መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደስሟ ውብ እና ማራኪ እንደሆነች እንደታዘቡ መግለፃቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመላክቷል፡፡

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች