በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተሰማሩ የ49 ኤጀንሲዎች ባለቤቶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ - ብሔራዊ መረጃ ማዕከል
በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተሰማሩ የ49 ኤጀንሲዎች ባለቤቶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዳስታወቀው፤ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን አስመልክቶ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ወንጀሉን በመፈፀም ላይ የሚገኙ አካላትንና የትስስር ሰንሰለታቸውን ለመለየት ሰፊ ጥናትና ክትትልና ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ጥናቱንና ክትትሉን መነሻ በማድረግ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በተከናወነው ስምሪት በድርጊቱ ሲሳተፉ ተደርሶባቸው የተጠረጠሩ የ49 ኤጀንሲዎች ባለቤቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
እንደ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ፤ መንግሥት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነቶችን በመፈራረም ዜጎች ጥቅማቸው ሳይጓደልና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ውጭ ለሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችል ሕጋዊ አሠራር ዘርግቷል፡፡ ይህን የሥራ ስምሪት የሚመራ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከማቋቋም በተጨማሪ ሕጋዊ ስርዓትን የሚያሳልጥ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ፤ ከ1ሺ ሁለት መቶ ለሚበልጡ ኤጀንሲዎች ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
ይሁንና በሕጋዊነት ሽፋን በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ላይ የተሰማሩ ኤጀንሲዎች መኖራቸው በጥናት መረጋገጡን መረጃው ጠቁሟል፡፡ በዚህም ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ በተከናወነው ሰፊ ጥናት ከነሐሴ 2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም ባሉት 11 ወራት ውስጥ ብቻ 15 ሺ ዜጎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገር መውጣታቸው ተረጋግጧል፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚንቀሳቀሱ ደላላዎች በዚህ የወንጀል ትስስር ውስጥ ተሳትፎ እንዳላቸው በጥናቱ የተለየ ሲሆን፤ በጥቅም ትሥሥር የሚሰጥ የቱሪስትና የሥራ ቪዛ ለድርጊቱ እንደሚውል እንዲሁም በኤምባሲዎች የሚሠሩ ግለሰቦችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት እንደሚሳተፉበትም ተጠቁሟል፡፡
በሁሉም የወንጀሉ ተዋንያን ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነትን ለማስፈን ስምሪት እየተከናወነ መሆኑም በመረጃው ተመላክቷል፡፡ በሌሎች ሀገራት የሚንቀሳቀሱ ሕገ-ወጥ ደላሎችንም ከውጭ አጋር አካላት ጋር በተመሠረተው ትብብር አማካኝነት ጭምር ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሠራ ተጠቁሟል፡፡
በሕገ-ወጥ መንገድ የሚከናወኑ የሥራ ስምሪቶች ኢትዮጵያዊያንን ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፤ ለሥነ-ልቦናዊ ጉዳት፤ ለአስገድዶ መደፈር እንዲሁም ለአካል ክፍሎች ስርቆትና ለሞት እየተዳረጉ ይገኛል ያለው መረጃው፤ ሕጋዊ ፈቃዳቸውን ሽፋን በማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ ዜጎች ከሀገር እንዲወጡ የሚደረገው የተቀናጀ የወንጀል ድርጊት ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን 11 ሚሊዮን ዶላር ማሳጣቱን አመላክቷል፡፡
በመንግሥት መዋቅር የሚሠሩ አንዳንድ ግለሰቦች የጥቅም ትስስር በመፍጠር ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሉ ተባባሪ እንደሚሆኑ ጥናቱን ዋቢ በማድረግ የገለጸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ፤ ዜጎች በባሕር፣በየብስና በአየር ተጓጉዘው ወደ ውጭ ሀገራት ካቀኑ በኋላ በአንድ ማዕከል ተጠርንፈው ከአሠሪዎች ጋር በሚደረግ ድርድር ለሽያጭ እየቀረቡ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
ይህ ከሞራልና ከሕግ ያፈነገጠ ድርጊት የሀገርን ገጽታና መልካም ስም ከማጉደፍ ባሻገር ያልፍልናል ብለው የሚሰደዱ ወጣቶችን እንዲሁም በልጆቻቸው ተስፋ በማድረግ ጥሪታቸውን እየሸጡና እየተበደሩ የሚልኩ ወላጆችን ለከፍተኛ ሰቆቃ እየዳረገ በመሆኑ በተከታታይ በሚከናወኑ ክትትሎች፣ ማጣራቶችና ስምሪቶች በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድም የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ አረጋግጧል፡፡ በዚህ መሰሉ ዜጎችን የሚበድልና ሀገርን የሚጎዳ የወንጀል ድርጊት ውስጥ በመሳተፍ ላይ ያሉ አካላት ሁሉ ከብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዕይታና ክትትል የተሰወሩ አለመሆናቸውን አውቀው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
ከሕዝብ አይንና ጆሮ የተሰወረ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም ያለው የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ መላው ኢትዮጵያዊያን ይህን መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን ለሚመለከታቸው የጸጥታና ደኅንነት አካላት በመጠቆም የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቋል፡፡ በቀጣይ የሚወሰዱ ተከታታይ እርምጃዎችንም ለኅብረተሰቡ እንደሚያሳውቅ ጠቁሟል፡፡
መንግሥት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት የተደራጀ፣ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጥ፣ ጥቅምንና መብትን የሚያስከብር ሕጋዊ አሠራር የዘረጋ በመሆኑ ዜጎች በውጭ ሀገራት ለሥራ ስምሪት መጓዝ ሲፈልጉ በተመቻቸው ዕድል መጠቀም እንደሚገባቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመልክቷል፡፡