ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በቀጣናዊ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እያከናወኗቸው ያሉ የትብብር ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኡጋንዳ የውጭ ደኅንነት ተቋም በቀጣናዊ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እያከናወኗቸው ያሉ የትብብር ሥራዎችን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ገምግመዋል።

 

የኢትዮጵያና ኡጋንዳ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት ቀደም ሲል በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የደኅንነትና የጸጥታ ስጋት የሆኑትን ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን፣ ሕገወጥ ታጣቂዎችንና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የደረሱትን የሁለትዮሽ ስምምነት በመተግበር የተገኙ ውጤቶች እና ቀጣይ መጠናከር ባሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር ነጥቦች ላይ ውይይት አድርገዋል።

 

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በኩል የውጭ መረጃ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር እንዲሁም በኡጋንዳ በኩል ደግሞ የውጭ ደኅንነት ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ጆሴፍ ኦኬሎ የጋራ ውይይቱን መርተዋል።

 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር፥ ኡጋንዳ ቀጣናዊ እና አካባቢያዊ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር በመሥራት ታሪካዊ ወዳጅ መሆኗን ገልፀው፤ የሀገሪቱ የውጭ አቻ የመረጃ ተቋም ከመረጃ ልውውጥና ከደኅንነት አኳያ ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጋር የጀመረውን አጋርነት አጠናክሮ ለመቀጠል እያሳያው ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

 

የኡጋንዳ የውጭ ደኅንነት ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ጆሴፍ ኦኬሎ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት እና በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እየሠራች መሆኑን፤ እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት የመረጃ ተቋማት ሕገወጦችን ተከታትለውና ለይተው ተጠያቂ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ምቹ መደላድል ለመፍጠር የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

 

ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት የዛሬ ሁለት ዓመት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው  ይታወሳል።

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች