የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰግድ መኮንን ለመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እጁን መስጠቱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

በአማራ ክልል በርካታ የታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች በመንግስት የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ሰላማዊ ሕይወት እየመሩ መሆኑን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል፡፡

 

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይሉ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩትን የፀጥታ ችግሮች በንግግርና በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በመንግስት ለታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች በተደጋጋሚ የሰላም አማራጮች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡   

 

ይሁንና በክልሎችም ሆነ በፌዴራል መንግስት እየቀረበ ያለው የሰላም አማራጭ እንዳይሳካ እና ወደ መሬት እንዳይወርድ በተለይም ደግሞ ውጭ ሆነው በትግሉ ስም ጥቅም የሚያግበሰብሱ አንዳንድ ጽንፈኛ የዲያስፖራ አባላት ሰብስበው በሚልኩት ረብጣ ዶላር እንዲሁም ንፁሃንን አግተውና በጭካኔ ገድለው በሚጠይቁት እና በሚዘርፉት ገንዘብ ጥቅም የሰከሩ አንዳንድ የታጣቂ ቡድን አባላትና አመራሮች የሰላሙን አማራጭ ሲገፉ መቆየታቸውን የጋራ ግብረ- ኃይሉ መግለጫ ያመላክታል፡፡

 

መግለጫው አያይዞም፤ ከጥቅም፣ ከጎጠኝነት እና ከገንዘብ ክፍፍል ጋር በተያያዘ በአብዛኛው በታጣቂ ቡድኑ አባላት እና በቡድኑ አመራሮች መካከል በሚፈጠር አተካራ እና የእርስ በእርስ መጠፋፋት የትግሉ ዓላማ ከመስመር ወጥቷል በሚል በራሳቸው በቡድኑ አባላት እና አመራሮችም ጭምር እየታየ እና እየተገለፀ መምጣቱ ክልሎችን ለግጭትና ለትርምስ እየዳረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

 

ይህን ተከትሎም ይላል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይሉ መግለጫ፤ ለመንግስት እጃቸውን በመስጠት ወደ ሰላማዊ ህይወት እየተቀላቀሉ ያሉ የታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል፡፡ በዛሬው ዕለትም በአማራ ክልል የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰግድ መኮንን ለመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እጁን መስጠቱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይሉ አስታውቋል፡፡

 

ግለሰቡ እጁን የሰጠው በፅንፈኛ ኃይሉ አመራሮች እና ታጣቂ ቡድን አባላት አማካኝነት በአማራ ክልል ህዝብ ላይ የሚፈፀሙ አሰቃቂ ግድያዎች፣ እገታዎች፣ አስገድዶ መድፈሮች፣ ለሕዝብ ጠቀሜታ የሚውሉ መሰረት ልማቶች ውድመት፣ አፈና እና ሌሎችም -ሰብአዊ ድርጊቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው እንደሆን በሰጠው ቃል ማረጋገጡን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

 

የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አክሎም ኮሎኔል አሰግድ መኮንን እጁን የሰጠው ከቅርብ አጃቢው ገበየሁ ወንድማገኝ ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር መሆኑን አስታውቆ፤ ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመቀላቀላቸው ትግሉ በአማራ ክልል ህዝብ ስም ቢካሄድም የጠራ ጥያቄ የሌለውና ክልሉን ለምስቅልቅል እና ለልማት እጦት እየዳረገ ያለ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ባሉ የተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት ማስፈፀሚያ በመጠለፉ ምክንያት እንደሆነ መግለጹን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

 

የጽንፈኛ ኃይሉን በሚመሩት በእስክንድር ነጋና በዘመነ ካሴ መካከል የተፈጠረው ሽኩቻ ህዝቡን የከፋ ዋጋ ከማስከፈል የዘለለ ወደ አንድ የሚመጣበት ዕድል ሊኖረው እንደማይችል መረዳቱንም ኮለኔል አሰግድ ገልጿል፡፡

 

በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት የክልሉ ህዝብ ለከፋ ማኀበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል መዳረጉን የገለፀው ኮሎኔል አሰግድ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል የሚል አቋም እንዳለው ተናግሯል፡፡ ተሳስተውና ተደናግረው ቡድኑን የተቀላቀሉ የፅነፈኛ ቡድኑ አባላትና አመራሮች መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው እጃቸውን እንዲሰጡም አሳስቧል፡፡

 

በመጨረሻም የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል የሰላምን አማራጭ በመግፋት አሁንም በትጥቅ ትግል በሚገፉ ኃይሎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እየገለፀ፤ በዚህ አጋጣሚ የሰላም አመራጭን ተቀብለው ለሚመጡ የታጣቂ ቡድን አመራሮች እና አባላት ግብረ ኃይሉ የሚያደርገውን ድጋፍና እና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡  

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች