በሙስና እና ብልሹ አሠራር የተጠረጠሩ 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አሠጣጥ ጋር በተያያዘ ከተገልጋዮች የሚነሱ ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ከመሰረቱ ለመፍታት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተወጣጣ ግብረ-ኃይል ሕገ ወጦችንና ሙሰኞችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ለረጅም ጊዜ የተቀናጀ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል ይላል ጉዳዩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን የተላከው መግለጫ።

በመሆኑም ከተቋማቱ የተወጣጣውና ጉዳዩን እየተከታተለ ያለው የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመግለጫው እንዳመለከተው፤ ተገልጋዮች በመደበኛ የመንግሥት ስርዓት የሚፈልጉትን የፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶችን በአፋጣኝና በአነስተኛ ዋጋ ማግኘት ሲችሉ፤ ተጠርጣሪዎች የፈጠሯቸው የተንዛዙና እና የተወሳሰቡ አሠራሮች ዜጎችን ለከፋ እንግልት ከመዳረግ ባሻገር ላልተገባ ወጪ ሲዳርጉ ነበር፡፡

 

ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ በሙስና ተግባር መሰመራታቸውና የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ እንደነበር ያመለከተው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተወጣጣው ግብረ-ኃይል ግለሰቦቹ በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የተሰጣቸውን ስልጣንና ሐላፊነት ወደ ጎን በመተው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ላልሆኑ የውጭ ሀገራት ዜጎች፣ በወንጀል ተከሰው የጉዞ ሰነዳቸው ለታገደባቸውና ሐሰተኛ የማንነት መገለጫ ላላቸው ሕገወጦች ጭምር የፓስፖርት፣ ሊሴፓሴና ቪዛ አየር በአየር በመሸጥ እና በማስተላለፍ፤ መንገደኞች በሌሉበት ጉዞ እንዳላቸው በማስመሰል እና የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደተዘዋወሩ የሚገለፅ ማሕተም በማዘጋጀት ተግባር ተሰማርተው ተገኝተዋል።

 

በተጨማሪም ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ተመልምለው ያለፉ እንደሆኑ በማስመሰል ግለሰቦች ባልተገባ መንገድ ለሥራ ወደ ተለያዩ የዓረብ ሀገራት እንዲወጡ በማድረግ እንዲሁም የሕጋዊ ግለሰብን ፓስፖርት ፎቶግራፍ በመቀየር ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ እንደተደረሰባቸው የግብረ-ኃይሉ መግለጫ ጠቁሟል።

 

እነዚህ ወንጀለኞች ከአዲስ አበባ እስከ ክልሎች የጥቅም ትስስር በመዘርጋት ሙስና ሲፈጽሙ ከመቆየታቸውም ባሻገር፤ ሐሰተኛ የማንነት መታወቂያዎችን በማዘጋጀት ተግባር ላይ ተሰማርተው ከነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ጋርም ግንኙነት በመፍጠር ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደቆዩ ታውቋል።

 

ይህን ተከትሎም ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተወጣጣው ግብረ-ኃይሉ ባደረገው ክትትል 200 በላይ የሚሆኑ በሕገወጥ መንገድ የተዘጋጁ ፓስፖርቶች እንዲመክኑ የተደረገ ሲሆን፤ የወንጀል ድርጊቱም መንግሥትን በሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ እንዳሳጣው በመግለጫው ተመልክቷል።

 

በጉዳዩ ላይ ምርመራ ሲያደርግ የቆየው ግብረ -ኃይሉ መግለጫ እንዳመለከተው፤ በአዲስ አበባ ከተማ፤ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በወንጀሉ የተሳተፉ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሲያገለግሉ የነበሩ ከከፍተኛ አመራርነት እስከ ባለሙያ ያሉ 42 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

 

በዙሁ መሰረትም በወንጀል ድርጊቱ ተሰማርተው ከተገኙና በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከልም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ታምሩ ግንበቶ አዋልሶን ጨምሮ ዘመድኩን ጌታቸው፣ ከድር ሰዒድ ስሩር፣ አስቻለው እዘዘው፣ አብዱላሂ አሊ መሀመድ (አብዱላሂ ጃርሶ) ቴዎድሮስ ቦጋለ፣ ጌትነት አየለ፣ ጀማል ገዳ፣ ሙላት ደስታ፣ ጅላሎ በድሩ፣ ገነት /ማርያም፣ ደገፋ ቤኩማ ወንድይፍራው ሽመልስ /ሰንበት እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተወጣጣው ግብረ-ኃይል አስታውቋል። በተያዙት ተጠርጣሪዎች ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽም፤ በግለሰቦቹ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ያላቸው ዜጎች ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉም ገልጿል፡፡

 

በዚህ ኦፕሬሽንም የተለያዩ ፓስፖርቶች፣ የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች፣ ሐሰተኛ መታወቂያዎች፣ አየር በአየር የወጡ ሊሴ ፓሴዎችና የታተሙ ቪዛ ካርዶች በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤትና የሥራ ቦታ በተደረገ ብርበራ በኢግዝቢትነት መያዛቸወን ግብረ -ኃይሉ አመልክቷል።

 

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተወጣጣው ግብረ -ኃይል በእንደዚህ አይነት ሕገ ወጥ ተግባር ዙሪያ የሚያካሂደውን ምርመራ፣ ክትትልና ኦፕሬሽን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፤ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ማኅበረሰቡ ላሳየው የተለመደና ቀና ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ 

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች