በአሸባሪዎች የሚወጠኑ የጥፋት እቅዶች የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ መቻሉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

በአሸባሪዎች የሚወጠኑ የጥፋት እቅዶች የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ መቻሉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ

 

የመረጃ ስምሪት ሽፋንና ጥራት በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ በአሸባሪዎች የሚወጠኑ የጥፋት እቅዶች የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ መቻሉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም በተገመገመበት መድረክ የተገኙት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዳስታወቁት፤ በተቋማዊ ሪፎርሙ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚደረገውን የመረጃ ስምሪት ሽፋንና ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል፡፡

 

በተለይ 2014 የሥራ ዘመን መረጃን በስፋት፣ በፍጥነትና በጥራት ለመሰብሰብ የሚያግዙ ዘመናዊ መሣሪያዎች ተሟልተው ወደ ስምሪት በመግባታቸው አሸባሪዎች፣ ህገወጥ ታጣቂ ቡድኖች፣ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈፅሙ አካላት፣ በጥቅሉ ፀረ-ሰላም እና ዕድገት ቡድኖች የሀገራችንንና ህዝባችንን ሰላም ለማደፍረስና የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማቀጨጭ የነበራቸው የተቀናጀ ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ እገዛ አድርገዋል፡፡

 

የመረጃ ስምሪት ሽፋንና ጥራትን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉ በኢትዮጵያ የውጭና የውስጥ ጠላቶች የጋራ ትብብር የሚወጠኑ የጥፋት እቅዶችም የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት እንዳይሆኑ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን ዳይሬክተር ጀነራሉ ገልጸዋል፡፡

 

አልሸባብ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በመለመላቸውና ሥልጠና እየሰጠ ለማሥረግ በሞከራቸው አባላቱ ዙሪያ በተደረገ ክትትል በርካታ አባላቱ ከመደምሰሳቸውም በተጨማሪ ተጠርጣሪዎችና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን የጠቆሙት አቶ ተመስገን፤ ከሸኔ ጋር በትብብር ለመንቀሳቀስ ያደረጋቸውን ሙከራዎችም ማክሸፍ መቻሉን አመልክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የአይ ኤስ የሽብር ቡድንን ተልዕኮ ተቀብለው ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት የሞከሩ አሸባሪዎች ከተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

 

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞችና ጸረ ሰላም ታጣቂ ቡድኖች ዙሪያ በተጠናቀሩ መረጃዎች አማካኝነትም እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በዕቅድ ዘመኑ ተቀባይነቱንና ተሰሚነቱን የሚያጎሉ፤ በዜጎች ዘንድ መተማመንን የሚፈጥሩ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መንቀሳቀሱን ያመለከቱት አቶ ተመስገን፤ ኅብረተሰቡ መረጃ በመስጠት የሚያሳየው ትብብር መጨመሩ፤ ክልሎችና ባለድርሻ አካላት የተቋሙን የመረጃ ውጤቶች በስፋት መፈለጋቸውና የውጭ አቻ ተቋማት በአጋርነት ለመሥራት ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱ ለዚህ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

 

‹‹በጠላት የሚፈራ በዜጎቹ የሚከበርና የሚወደድ ተቋም ለመገንባት እየተደረገ ያለው ጥረት ፍሬያማ እየሆነ ነው›› ያሉት አቶ ተመስገን፤ በተለይ በዕቅድ ዘመኑ በከፍተኛ ርብርብ እውን ሆኖ በበርካታ የሀገር ውስጥ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በውጭ ሀገራት የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የተጎበኘው ዲጂታል ኤግዚብሽን ይህን ገጽታ በመፍጠር ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

 

የጸደቀው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የማሻሻያ ዐዋጅ የሥነ ልቦና ጦርነትን በተደራጀ መንገድ የመምራት ሥልጣንን ለተቋሙ መስጠቱ፤ የሠራተኞች አስተዳደር ጉዳይን ማሻሻሉና አስፈጻሚ አካላት የመረጃ ግብዓቶችን ባለመጠቀማቸው ለሚከሰተው ችግር ተጠያቂ እንዲሆኑ መደንገጉ ተቋማዊ ተልእኮን በብቃት በመፈጸም እንዲሁም ወቅታዊ የደኅንነት ስጋቶችን በመመከት ረገድ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ዳይሬክተር ጀነራሉ አቶ ተመስገን አመልክተዋል፡፡

 

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በእቅድ ዘመኑ ብሔራዊ ደኅንነትንና ጥቅምን በማረጋገጥ ረገድ የመሪነት ሚናው ጎልቶ መወጣቱን ዳይሬክተር ጀነራሉ አስታውቀዋል፡፡ ከሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ጋር በተያያዘ ተደቅነው የነበሩ ስጋቶችን አስቀድሞ በጥናት በመለየት እንዲፈቱ የተሄደበት አግባብና ከፍተኛ ሀገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን ማክሸፍ የተቻለባቸውን ስኬቶች እንደ አብነት አንስተዋል፡፡

 

በተጠናቀቀው በጀት አመት አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በህልውና ዘመቻው አስቻይ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችንበማቅረብና ከጸጥታ ተቋማት ጋር በመናበብ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉ እንዲሁም የመረጃ ስምሪትን በአንድ ማዕከል በማስተዳደርና በማሰራጨት ያከናወነው የማስተባበር ሥራ ሽብርተኛ ቡድኖችና ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑ የውጭ ኃይሎችን ሀገር የማፍረስ ሴራ በማክሸፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል፡፡

 

የተቋሙን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና ሌሎችንም አማራጮች በመጠቀም ከፍተኛ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ስራዎች መከናወናቸውን፤ ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር የሚያስችሉ መጠነ ሰፊ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውንም አቶ ተመስገን ጠቁመዋል፡፡

 

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የአመቱ ስኬታማ ሥራዎች ስትራቴጂክ አመራሩ በመናበብና በመግባባት ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በጋራ ተቀናጅቶ ተልእኮዎችን በመምራቱ፤ አባሉም እስከ ሕይወት መስዋእትነት ጭምር በመክፈል ስምሪቶችን በመወጣቱ የተመዘገቡ ስለሆኑ ለሁሉም አክብሮትና ምስጋና ይገባል ያሉት አቶ ተመስገን፤ በቀጣይም ሀገራዊ ደኅንነትን፣ ብሔራዊ ጥቅምንና ክብርን ለማረጋገጥ ቀን ከሌት ኃላፊነትን ለመወጣት ርብርብ እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

 

ኅብረተሰቡም ለመረጃ ሥራ ተባባሪ በመሆን ወሳኝ ሚና ማበርከቱን በመጠቆም፤ የሀገርን ደኅንነት የመጠበቅ ጉዳይ የእኔም አስተዋጽዖ ውጤት ነው የሚለው አመለካከት መጎልበት ይገባዋል ብለዋል፡፡

 

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ‹‹ዘሬም እንደ ትናንቱ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን!›› የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር / ዐቢይ አሕመድ መልዕክት መነሻ በማድረግም የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ የተካሄደውን ዘመቻ ለመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር / ዐቢይ አሕመድ፤ ለኢትዮጵያ ህልውና መስዋዕትነት ለከፈሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል የፀጥታ አካላት፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አባላት እንዲሁምለመላው ኅብረተሰብ ምስጋናቸውን በመድረኩ አቅርበዋል፡፡

 

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች