የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን እውን ለማድረግ በድርድርና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን እውን ለማድረግ የጀመረችው በድርድርና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

 

‹‹የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ›› በሚል ርዕስ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ‹‹የድንበርና ድንበር ተሸጋሪ የውሃ ሀብቶችን መሠረት ያደረጉ ለባሕር በር ድርድር የሚረዱ ጠቋሚ ሐሳቦች፤ የባሕር በር ጉዳዮች ከዓለም አቀፍ ሕግና ፖሊሲ አንጻር እንዲሁም ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከሶማሌላንድ ጋር የመተባበር ባለብዙ ዘርፍ አማራጭነት›› በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በዘርፉ ምሁራን የጥናት ውጤቶችን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን ሕግጋት ባከበረ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበርና አብሮ በማድግ ላይ የተመሠረተ የባሕር በር ጥያቄዋን አጠናክራ መቀጠል እንደሚገባት ነው ጥናት አቅራቢዎች የጠቆሙት፡፡

 

ጥናቶቹ ተሰንደው ለውሳኔ ሰጪ አካላት ግብአት ሆኖ ሊያገለግሉ እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

በሲምፖዚየሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ፤ በታሪክና በሕግ የባሕር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ሕጋዊና ታሪካዊ መብቷን ተነፍጋ ከባሕር ተከልላ ለመኖር ተገዳለች ብለዋል፡፡

 

አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ኢትዮጵያ ከባሕር በር ተከልላ ልትቀጥል የማትችልበት ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቁመዋል፡፡

 

አራት መሰረታዊ ጉዳዮች የባሕር በር ጥያቄውን አንገብጋቢ ያደርጉታል ያሉት አቶ ሲሳይ፣ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ እድገት፤ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ቁጥርና የሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፤ ሕጋዊና ታሪካዊ የባሕር በር የባለቤትነት ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗ እንዲሁም ለባሕር በር ያላት መልክዓ ምድራዊ ቀረቤታ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ የምታነሳው የባሕር በር ተጠቃሚነት እና የባለቤትነት መብት የተናጠል ተጠቃሚነት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ያሉት አቶ ሲሳይ፤ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነትም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረና ቀጣናው አብሮ እንዲያድግ አስተዋጽዖ የሚያበረክት ፀጋ እንጂ ሀገራትን በመጉዳት ላይ የተንጠለጠለ ሥጋት አለመሆኑ ለማንም ግልጽ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

 

ይሁን እንጅ የሀገራችን ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶች አጀንዳውን በተሳሳተ መንገድ በማራገብ ቀጣናውን ለማተራመስ እንደ ምክንያት ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ እያስተዋልን እንገኛለን ሲሉም ተናግረዋል።

 

በዚህ ረገድ ለሶማሊያ መንግሥትም ሆነ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ እውነታውን በማስረዳትና የተዛቡ አመለካከቶች እንዲቀረፉ በማድረግ በኩል ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡና ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

 

ሀገራችን የያዘችውን ወርቃማ እውነት ለዓለም በማሳወቅ ረገድ መንግሥታዊና የግል የመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም በማንኛውም የማሕበራዊ ሚዲያ አውታር ተሳትፎ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ያላሳለሰ ጥረት በማድረግ ታሪካዊ ሐላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፤ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ብቸኛ እንደማይሆንና ወደ ውጤት ለመቀየርም በቂ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ስምምነቱ ስለ ባሕር በር ጥያቄ ማቅረብ የማይደፈር ሆኖ የቆየበትን የተዛባ አስተሳሰብ የሰበረ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ስትራቴጂክ ጥቅሞቻችን ለማስከበር እንድንችል በር የከፈተ ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡

 

በሲምፖዚየሙ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፀጥታ፣ ደኅንነትና የሌሎች ተቋማት የሥራ ሐላፊዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ተጋባዥ እንግዶች መታደማቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።

 

Asset Publisher

የቅርብ ዜናዎች