በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 50 ተጠርጠሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ:- የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል - ብሔራዊ መረጃ ማዕከል
በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 50 ተጠርጠሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ:- የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል
በአዲስ አበባ እና አዋሳኝ አካባቢዎች በትጥቅ የታገዘ ሁከት እና ብጥብጥ ለመፈፀም በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 50 ተጠርጠሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ ።
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ይህ የጥፋት ቡድን ቀደም ሲል አማራ ክልልን የነውጥ እና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የነበረው የጥፋት ሴራ በክልሉ የፀጥታ ሀይል፡ በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል መንግስት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ስለከሸፈበት፤ይሄንኑ እኩይ ዓላማውን ወደ ማዕከል በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በማምጣት የሁከትና የሽብር ተልዕኮው መፈፀሚያ የማድረግ እኩይ ሴራ መሆኑን ግብረ ሀይሉ ጠቅሷል፡፡
መግለጫው አክሎም፤በቁጥጥር ስር የዋለው የተደራጀው የህቡዕ ቡድን ዋና ማዕከሉን አዲስ አበባ እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ በማድረግ በልዩ ሁኔታ ያዘጋጀውን የታጠቀ ኃይል ከህቡዕ ቡድኑ ጋር በማስተሳሰር በተናበበ እና በተቀናጀ መንገድ አዲስ አበባንና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችን የሁከት የብጥብጥ እና የሽብር ሴራው ኢላማ የማድረግ እኩይ ተልዕኮ አንግቦ ሲሰራ ቆይተዋል፡፡
ቡድኑ ለአደረጃጀቱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥሩልኛል የሚላቸውን አንዳንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮችን በመጠቀም ተቋማትን መሰብሰቢያ እና ማደራጃ በማድረግ በህቡዕ ሲንቀሳቀስ እንደነበር መረጋገጡን መግለጫው አመልክቷል፡፡
በህቡዕ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቡድኑ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች አባላትን የመመልመልና እና ሎጀስቲክስ የማደራጀት ሥራዎችን ሲያከናውን እንደቆየ የጠቆመው መግለጫው፤ ቡድኑ በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የጥፋት መረብ ዘርግቶ ከሚንቀሳቀሰው ፀረ ሰላም ሀይል ጋር የህቡዕ ትስስር በመፍጠር እና ተልዕኮ በመቀበል አዲስ አበባ እና የኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎችንም ጭምር የድብቅ ሴራው አካል አድርጎ ሲንቀሳቀስ በዋናነት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባለፉት አምስት ወራት ባካሄደው ጥብቅና ሚስጥራዊ ክትትል እንደተደረሰበትና የክትትል ግኝቱም ለጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ቀርቦ ከተገመገመ በኋላ ወደ ተቀናጀ ኦፕሬሽን በመግባት በተጠርጠሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን መግለጫው አመልክቷል፡፡
ለቡድኑ በአዲስ አበባና በአዋሳኝ አካባቢዎች እኩይ ተግባር እንዲፈፅም የጥፋት ተልዕኮ የሰጡት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ሀይሎች በክልሉ በትጥቅ የታገዘ ጥቃት በንፁሃን፣በመንግስት አካላትና በፀጥታ ሀይሎች ላይም ጭምር በመፈፀም መንግስትን በኃይል ከስልጣን ለማስወገድ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ያለው የጋራ ግብረ ሀይሉ መግለጫ፤ ይህ እኩይ ሴራቸው በመንግስት ፀጥታ ሀይሎች በመክሸፉ እና በዚህም የቁም ቅዥት ውስጥ በመግባታቸው የተሰጣቸውን ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ ከመጠቀም ይልቅ አሁንም በህገ ወጥ ተግባራቸው በመቀጠላቸው በመንግስት ፀጥታ ሀይሎች የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
የህቡዕ አደረጃጀት ፈጥሮ የነበረው ይህ ቡድንና ተባባሪዎቹም፤ በትጥቅ የታገዘ ሁከት እና ብጥብጥ በአዲስ አበባና በአዋሳኝ አካባቢዎች ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ ተተኳሾች፣ ቦንቦች፣ ተቀጣጣይ ቁሶች እንዲሁም የተከማቹ ለቡድኑ የቀለብ አገልግሎት የሚውሉ ልዩ ልዩ ግብአቶች፣ የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች፣ የባንክ ደብተሮች እና የተለያዩ ሰነዶች ጋር መያዛቸውን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት 50 ተጠርጣሪዎች ውስጥም የቡድኑ መሪ ስንታየሁ ንጋቱ ገብረ እየሱስ በቅፅል ስሙ አብርሃም እንዲሁም ለቡድኑ ፋይናንስ፡ ሎጀስቲክስና ሃብት አፈላላጊ አመራር ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ፋሲል ጌታቸው እና ተወልደ ብርሀን የተባሉ ተጠርጣሪዎችም እንደሚገኙበት የጋራ ግብረ ሀይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሴራው ዋነኛ ጠንሳሾች በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚገኙ የቡድኑ አስተባባሪዎች በዋናነትም ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፡ ሀብታሙ አያሌው እና መሳይ መኮንን እንዲሁም በሀገር ውስጥ በእስክንድር ነጋ የሚመራው የጥፋት ሃይል እና ቀደም ሲል ቡድኑን በበላይነት ሲመሩ የነበሩት በአሁኑ ሰዓት በህግ ቁጥጥር ሥር በማረሚያ ቤት የሚገኙ የእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፡ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው እና ዮርዳኖስ ዓለሜ የሚመራ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።
ህቡዕ ቡድኑ አደረጃጀቱን ከህዳር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሰነድ በማዘጋጀትና የጋራ መግባባት በመፍጠር የራሱ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ የመረጃ እና ፋይናንስ እንዲሁም የሚዲያ እና የፕሮፖጋንዳ ክንፍ የሚል መዋቅር በመፍጠር ሲንቀሳቀስ መቆየቱንም ግብረ-ኃይሉ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል፤ የእምነት ተቋማት አማኙ በቅንነት ሄዶ የእምነት ስራውን የሚፈፅምባቸው መሆኑን በመረዳት እኩይ ዓላማ ያላቸው የጥፋት ሀይሎች የእምነት ቦታዎችን ለጥፋት ተልዕኮ እየተጠቀሙበት በመሆኑ፤ህብረተሰቡም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ከእምነቱ ስርዓት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥብቁ ቁጥጥርና እና የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው ግብረ ሀይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ህዝቡም ከፀጥታና ደኅንነት አካላት ጎን በመቆም የጥፋት ሀይሎችን ለማጋለጥ የጠለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ግብረ ሀይሉ ጠይቋል፡፡
ፀረ ሰላም ሀይሎች በተደጋጋሚ የሚያደርጓቸው የጥፋት ሴራዎች ከፀጥታና ደኅንነት አካላት አይንና ጆሮ የማያመልጡ መሆኑን አውቀው፤ ከጥፋት መንገዳቸው ተመልሰው መንግስት ያዘጋጀውን የሰላም አማራጭ እንዲጠቀሙበት የጋራ ግብረ ሀይሉ ያሳስባል፡፡
ለዚህና መሰል የጥፋት ተልዕኮዎች መሳሪያ እየሆኑ ያሉ ንፁሃን ዜጎችም ራሳቸውን ከእንደዚህ ዓይነቱ ድርጊት እንዲቆጠቡ ይመክራል፡፡
ለጥፋት ሀይሎች የፋይናንስና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን በማድረግ ሀገሪቱን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ እየሰሩ ሀይሎች ከእኩይ ዓላማቸው እንዲቆጠቡ በዚህ አጋጣሚ ግብረ ሀይሉ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም ለኦፕሬሽኑ መሳካት ማህበረሰቡ ለፀጥታና ደኅንነት ግብረ -ኃይሉ ላሳየው ጠንካራ ድጋፍ እና የዘወትር ትብብር የጋራ ግብረሃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
በቀጣይም የእነዚህን ፀረ ሰላም ሀይሎች እኩይ የጥፋት ዓላማ በማክሸፍ በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በመደገፍና ወንጀለኞችን በማጋለጥ ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በመጨረሻም በፀረ-ሰላም ሀይሎች የታቀዱ የጥፋት ሴራዎችን በማክሸፍ እና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ በኩል የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ፣የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት መሆኑን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል እያሳወቀ፤ እርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የጋራ ግብረ- ኃይሉ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አረጋግጧል፡፡
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል
መጋቢት 10/2016 ዓ.ም